
መጽሐፍ ቅዱስ — Unlocked Literal Bible
የኖኅ መርከብ በመጽሐፍ ቅዱስ፦
የዘፍጥረት 6–9 ቃል
ስለ ኖኅ መርከብና ስለ ጥፋት ውኃ የሚናገረውን ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 እስከ 9 በቁጥር ተደራጅቶ ለቤተሰብ ንባብ ያንብቡ።
Genesis · መጽሐፍ ቅዱስ — Unlocked Literal Bible
ምዕራፍ 6
- የሰው ልጆች በምድር ላይ እየበዙ ሲሄዱ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው።
- የእግዚአብሔር ልጆችም የሰዎች ሴቶች ልጆች የሚስብ ውበት እንዳላቸው ተመለከቱ። ከእነርሱ መካከልም የመረጧቸውን ሚስቶች አድርገው ወሰዱ።
- እግዚአብሔርም፦ “እርሱ ሥጋ ስለሆነ መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፤ ዕድሜውም 120 ዓመት ይሆናል” አለ።
- የእግዚአብሔር ልጆች ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋብቻ በፈጸሙና ልጆችን በወለዱበት በዚያን ጊዜ ከዚያም በኋላ ኔፊሊም የተባሉ ግዙፍ ሰዎች በምድር ላይ ነበሩ። እነርሱም በጥንት ዘመን ዝናን ያተረፉ ኅያላን ነበሩ።
- እግዚአብሔር የሰው ልጆች ክፋት በምድር ላይ እየበዛ እንደሆነና የልቡም ሃሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ።
- እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ ልቡም አዘነ።
- በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር፦ “የፈጠርሁትን የሰው ልጅ ከምድር ገጽ አጠፋለሁ፤ ስለፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና ከእነርሱም ጋር እንስሳትን፣ በደረታቸው የሚሳቡትን ፍጥረታትና የሰማይ ወፎችን ሁሉ አጠፋለሁ” አለ።
- ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አገኘ።
- የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው። ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ከበደል የራቀ ሰው ነበር፤ የእግዚአብሔርንም መንገድ የሚከተል ሰው ነበር።
- ኖኅ ሴም፣ ካምና ያፌት የተባሉትን ሶስት ወንዶች ልጆች ወለደ።
- በእግዚአብሔር ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች በዓመፅም ተሞላች።
- እግዚአብሔር ምድርን ተመለከተ፣ የተበላሸች እንደሆነችና በምድር የሚኖሩትም ሰዎች ሁሉ በክፋት እንደሚኖሩ አየ።
- እግዚአብሔርም ኖኅን፦ “ሥጋን የለበሰ ሁሉ ፍጻሜ ደርሶአል፣ ከእነርሱ የተነሳ ምድር በግፍ ተሞልታለችና። እኔም በእርግጥ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ።
- አንተ ግን ከጥሩ እንጨት መርከብ ሥራ፤ መርከቧም ክፍሎች እንዲኖራት አድርግ፤ ውስጧንና ውጭዋንም በቅጥራን ለቅልቀው።
- እንደዚህ አድርገህ ሥራት፦ ርዝመቷ 140 ሜትር፣ ወርዷ 23 ሜትር፣ ከፍታዋ 13. 5 ሜትር ይሁን።
- ለመርከቧ ጣራ አብጅላት፣ ጣራና ግድግዳው በሚጋጠምበት ቦታ ግማሽ ሜትር ክፍተት ተው፤ ከጎኗ በር አውጣላት፤ ባለ ሦስት ፎቅ አድርገህ ሥራት።
- እኔም ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለባችውን ፍጡራን ሁሉ ለማጥፋት እነሆ በምድር ላይ የጥፋት ውሃ አወርዳለሁ፤ በምድር ላይ ያለ ሁሉ ይጠፋል።
- ከአንተ ጋር ግን ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከአንተ ጋር ወደ መርከቧ ትገባላችሁ።
- ከአንተ ጋር በሕይወት እንዲቆዩ ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ወንድና ሴት እያደረግህ ሁለት ሁለቱን ወደ መርከቧ ታስገባለህ።
- ከእያንዳንዱ የወፍ ወገን፣ ከእያንዳንዱ የእንስሳ ወገን፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረት ሁሉ በየወገናቸው በሕይወት ይቆዩ ዘንድ ወደ አንተ ይምጡ።
- ለአንተና ለእነዚህ ፍጥረቶች ሁሉ የሚበቃ ልዩ ልዩ ዓይነት ምግብ በመርከቡ ውስጥ አከማች።”
- ኖኅም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።
Genesis · መጽሐፍ ቅዱስ — Unlocked Literal Bible
ምዕራፍ 7
- እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፦ “በዚህ ትውልድ መካከል አንተን ጻድቅ ሆነህ አግኝቼሃለሁና ቤተሰብህን በሙሉ ይዘህ ወደ መርከቧ ግባ።
- ከንፁህ እንስሳት ሁሉ ሰባት ሰባት ወንድና ሴት፣ ንፁሕ ካልሆኑት እንስሳት ደግሞ ሁለት ሁለት ወንድና ሴት ከአንተ ጋር አስገባ።
- እንዲሁም ከሰማይ ወፎች ወገን ሰባት ወንዶችና ሰባት ሴቶች በምድር ላይ ለዘር እንዲተርፉ ከአንተ ጋር ታስገባለህ።
- ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በመድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁ፤ የፈጠርሁትንም ሕያው ፍጡር ሁሉ ከምድር ላይ አጠፋለሁ።”
- ኖኅም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።
- የጥፋት ውሃ በምድር ላይ በወረደ ጊዜ ኖኅ የ600 ዓመት ሰው ነበር።
- ኖኅና ወንዶች ልጆቹ ሚስቱና የልጆቹ ሚስቶች ከጥፋት ውሃ ለማምለጥ ወደ መርከቡ ገቡ።
- ንፁሕ ከሆኑትና ንፁሕ ካልሆኑት እንስሳት ከወፎችና በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ
- ጥንድ ጥንድ ወንድና ሴት ሆነው ወደ ኖኅ መጡ፤ እግዚአብሄር ኖኅን ባዘዘው መሠረትም ወደ መርከቧ ገቡ።
- ከሰባት ቀንም በኋላ የጠፋት ውሃ በምድር ላይ መጣ።
- ኖኅ በተወለደ በ600ኛው ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ቀን የታላቁ ጥልቅ ምንጮች በሙሉ ተነደሉ፤ የሰማይ መስኮቶችም ተከፈቱ።
- ዝናቡም መዝነብ ጀመረ፣ አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ባለማቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ።
- ዝናቡ መዝነብ በጀመረበት ቀን ኖኅና ሚስቱ ከልጆቻቸው ጋር ከሴም ከካም ከያፌትና ከሶስቱም ልጆቻቸው ሚስቶች ጋር ወደ መርከቡ ገቡ።
- ከአራዊት ከእንስሳት በደረታቸው እየተሳቡ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችና በሰማይ ከሚበሩ ወፎች ከእያንዳንዱ ዓይነት አብረዋቸው ገቡ።
- የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸው ፍጡራን በሙሉ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ከኖኅ ጋር ወደ መርከቡ ገቡ።
- ከሕያዋንም ፍጡራን ሁሉ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘው መሠረት ወንድና ሴት እየሆኑ ገቡ፤ ከዚያም እግዚአብሔር የመርከቡን በር ከውጭ ዘጋ።
- የጥፋት ውሃም ለአርባ ቀናት ያለመቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ ውሃው እየጨመረ በሄድ መጠን መርከቧን ከምድር ወደ ላይ አነሳት።
- ውሃው በምድር ላይ በጣም እየጨመረና ከፍ እያለ ሲሄድ፣ መርከቧ በውሃ ላይ ተንሳፈፈች።
- ውሃው በጣም ከፍ በማለቱ፣ ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራሮች ሁሉ ሸፈናቸው።
- ውሃው ከተራሮች ጫፍ በላይ 7ሜትር ያህል ከፍ አለ።
- በምድር ላይ የነበሩ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፦ ወፎች፣ የቤት እንስሳት፣ አራዊት፣ በምድር የሚርመሰመሱ ፍጡራን ሰዎችም በሙሉ ጠፉ።
- የሕይወት እስትንፋስ ያላቸው በምድር የነበሩ ፍጡራን ሁሉ ሞቱ።
- ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ሁሉ ከሰዎች ጀምሮ እንስሳት፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንና የሰማይ ወፎች ሁሉም ከምድር ገጽ ጠፉ። ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከቧ ውስጥ የነበሩት ብቻ ተረፉ።
- ውሃውም ምድርን ሸፍኖ መቶ አምሳ ቀን ቆየ።
Genesis · መጽሐፍ ቅዱስ — Unlocked Literal Bible
ምዕራፍ 8
- እግዚአብሔር ኖኅንና ከእርሱ ጋር በመርከቧ ውስጥ የነበሩትን አራዊትና እንስሳት ሁሉ አሰበ። በምድር ላይ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ ውሃውም ጎደለ።
- የጥልቁ ምንጮችና የሰማይ መስኮቶች ተዘጉ፣ ዝናቡም መዝነቡን አቆመ።
- ውሃው ከምድር ላይ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ፤ ከመቶ ሃምሳ ቀን በኋላም የውሃው ከፍታ እጅግ ቀነሰ።
- በሰባተኛው ወር፤ በአሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቧ በአራራት ተራሮች ላይ አረፈች።
- ውሃው እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ቀስ በቀስ እየጎደለ ሄደ። በአሥረኛው ወር መጀመሪያው ቀን የተራሮች ጫፎች ታዩ።
- ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቧን መስኮት ከፍቶ፣
- ቁራን ወደ ውጭ ላከ፤ ቁራውም ውሃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር።
- ከዚያም በኋላ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ ገጽ ጎድሎ እንደሆነ ለማወቅ ርግብን ላከ፤
- ነገር ግን ውሃው ገና ምድርን ሁሉ ሸፍኖ ስለነበር ርግቢቱ የምታርፍበት ቦታ አላገኘችም፤ ስለዚህ ኖኅ ወዳለበት መርከብ ተመልሳ መጣች፤ ኖኅም እጁን ዘርግቶ ወደ መርከቡ ውስጥ አስገባት።
- ሰባት ቀን ከቆየ በኋላ ኖኅ ርግቧን እንደገና ላካት።
- እርሷም ወደ ማታ ተመለሰች፤ እነሆም የለመለመ የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጉደሉን አወቀ።
- ደግሞም ሰባት ቀን ከቆየ በኋላ ኖኅ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት፤ በዚህ ጊዜ ግን ርግቢቱ ወደ እርሱ አልተመለሰችም።
- ኖኅ በተወለደ 601ኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውሃው ከምድር ላይ ደረቀ። ኖኅ የመርከቡን ክዳን አንሥቶ ዙሪያውን ተመለከተ፣ ምድሪቱም እንደደረቀች አየ።
- በሁለተኛው ወር፣ በሃያ ሰባተኛው ቀን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ደረቀች።
- ከዚያም እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው።
- “አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቧ ውጡ።
- እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲበዙ ከአንተ ጋር ያሉትን ወፎች፣ እንስሳትና በምድር ላይ የሚሳቡ ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ይዘሃቸው ውጣ።”
- ስለዚህ ኖኅ ከልጆቹ፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ወጣ።
- እንስሳቱ ሁሉ፣ ወፎችም፣ በምድር የሚሳቡት፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ በየወገናቸው ከመርከቧ ወጡ።
- ኖኅም ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ። ንፁሕ ከሆኑት እንስሳትና ንፁሕ ከሆኑት ወፎች አንዳንዶቹን ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።
- እግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን መዓዛ አሸተተ፣ በልቡም እንዲህ አለ፦ “ምንም እንኳ ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ ቢሆንም በእርሱ ምክንያት ሁለተኛ ምድርን አልረግማትም፤ አሁን እንዳደረግሁት ሕያዋን ፍጡራንን ዳግመኛ አላጠፋም።
- ምድር እስካለች ድረስ የዘር ወቅትና መከር፣ ሙቀትና ቅዝቃዜ፣ በጋና ክረምት፣ ቀንና ሌሊት አይቋረጡም።”
Genesis · መጽሐፍ ቅዱስ — Unlocked Literal Bible
ምዕራፍ 9
- ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ኖኅንና ልጆቹን እንዲህ ሲል ባረካቸው፦ “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት፤
- አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በእንስሳት፣ በሰማይ ወፎች፣ በደረት በሚሳቡ ተንቀሳቃሽ ፍጡሮችና በባሕር ዓሦች፣ በምድር ላይ በሚገኙ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ላይ ይሁን። ሁሉም በሥልጣናችሁ ሥር ይሁኑ።
- ሕያውና ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ፣ ለምለሙን ዕፅዋት እንደሰጠኋችሁ፣ አሁን ደግሞ ሁሉን ሰጠኋችሁ።
- ነገር ግን ሕይወቱ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ።
- ሰውን የገደለ ሁሉ ስለሟቹ ደም ተጠያቂ ነው፤ የሟቹን ሰው ደም ከገዳዩ ከእንስሳም ይሁን ከሰው እሻለሁ።
- የሰውን ደም የሚያፈስ ሁሉ ደሙ በሰው እጅ ይፈሳል፤ በእግዚአብሔር አምሳል እግዚአብሔር ሰውን ሠርቶታልና።
- እናንተ ግን ብዙ ተባዙ፣ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ ይንሠራፋም።”
- ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ለኖኅና ለልጆቹ እንዲህ አላቸው፦
- “እነሆ ከእናንተና ከእናንተ በኋላ ከሚመጣው ዘራችሁ ጋር ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤
- እንዲሁም ከእናንተ ጋር ከነበሩት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ከወፎች፣ ከእንስሳት ከእናንተ ጋር ከመርከቧ ከወጡት በምድር ላይ ካሉት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ኪዳን እገባለሁ።
- ከእንግዲህ ሕይወት ያለው ፍጡር ሁሉ በጥፋት ውሃ እንደማይጠፋ፣ ዳግመኛም ምድርን የሚያጠፋ ውሃ ከቶ እንደማይመጣ ከእናንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ።”
- እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፦ “በእኔና በእናንተ መካከል ከእናንተም ጋር ካሉ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፣ ከሚመጣው ትውልድ ሁሉ ጋር፣ የማደርገው የኪዳኑ ምልክት ይህ ነው፤
- ቀስተ ደመናዬን በደመና ላይ አድርጋለሁ፤ ይህም በእኔና በምድር መካከል ለገባሁት ኪዳን ምልክት ይሆናል።
- ደመናን በምድር ላይ በጋረድሁና ቀስቴም በደመና ላይ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ
- ከእናንተና ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር የገባሁትን ኪዳን አስባለሁ፤ ሕይወት ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ፣ ከእንግዲህ የጥፋት ውሃ ከቶ አይመጣም።
- ቀስቱ በደመና ላይ ተገልጦ በማይበት ጊዜ ሁሉ በእኔና በምድር ላይ ባሉ ሕያዋን ፍጡራን መካከል ያለውን ዘላለማዊ ኪዳን አስባለሁ።”
- ከዚያ በኋላም እግዚአብሔር ለኖኅ፦ “ይህ በእኔና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕያዋን ሁሉ መካከል የገባሁት ኪዳን ምልክት ነው።” አለው።
- ከመርከቧ የወጡትም የኖኅ ልጆች ሴም፣ ካምና ያፌት ነበር፤ ካም የከነዓን አባት ነው።
- እነዚህ ሶስቱ የኖኅ ልጆች ሲሆኑ፣ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ የተገኙት ከነዚሁ ነው።
- ኖኅ ገበሬ መሆን ጀመረ፣ ወይንንም ተከለ።
- ከወይኑም ጠጅ ጠጥቶ ሰከረና በድንኳኑ ውስጥ እርቃኑን ተኛ።
- የከንዓን አባት ካም የአባቱን ዕርቃነ ሥጋ አየ፤ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው።
- ሴምና ያፌት ግን ልብስ ወስደው በትከሻቸው ላይ አደረጉና የአባታቸውን ዕርቃነ ሥጋ እንዳያዩ ፊታቸውን አዙረው የኋሊት በመሄድ የአባታቸውን ዕርቃነ ሥጋ ሸፈኑ።
- ኖኅ ከወይን ጠጁ ስካር ሲነቃ ታናሽ ልጁ ያደረገበትን አወቀ።
- ከዚህም የተነሣ፦ “ከነዓን የተረገመ ይሁን፤ ለወንድሞቹም አገልጋይ ይሁን።” አለ።
- ደግሞም፦ “የሴም አምላክ የሆነው እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፣ ከነዓንም የሴም አገልጋይ ይሁን።
- እግዚአብሔር የያፌትን ግዛት ያስፋ፤ ያፌት በሴም ድንኳኖች ይኑር፤ ከነዓን የያፌት አገልጋይ ይሁን።” አለ።
- ኖኅ ከጥፋት ውሃ በኋላ 350 ዓመት ኖረ።
- ኖኅ በአጠቃላይ 950 ዓመት ኖሮ ሞተ።
የተያያዘ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት
ዘፍጥረት 6–9ን እያነበቡ ይቀቡ እና ይዳስሱ
የሚያነቡትን እያንዳንዱን ምዕራፍ ከ100 የA4 መቀቢያ ገጾች፣ ከ8 የኖኅ ቤተሰብ ሉሆች እና ከ3D ገጸ-ባህሪ ጥናቶች ጋር ያዛምዱ።